(አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1/2015 ዓ.ም) የዘንድሮው የአረጋውያን ቀን “የአረጋውያን ኢትዮጵያዊነት አሻራ ለትውልድ አደራ!” በሚል መሪ ቃል በአገራችን ለ31ኛ ጊዜ በዛሬው ዕለት በተለያዩ መርሀ ግብሮች በድምቀት ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝደንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ “መንግስት የአረጋውያንን ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ” ገልጸዋል፡፡
የአገር ባለውለታ ለሆኑ አረጋውያን ተገቢውን ትኩረት፣ ክብር፣ ድጋፍና ክብካቤ መስጠት ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቷ በመንግስት በኩል እየተደረገ ካለው ጥረት ባሻገር የአረጋውያንን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሉም እንዲሳተፍና የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ከሄልፕ ኤጅ ጋር በመተባበር በደመቀ መልኩ በዓሉ በተከበረበት ወቅት ሚኒስትሯ ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና ሌሎች የበጎ አድራጎት ተቋማት ተወካዮች ለአረጋውያን ያላቸውን ክብር ለመግለጽ እግር የማጠብ ስነስርዓት አስጀምረዋል፡፡
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን “የአረጋውያን የኢትዮጵያዊነት አሻራ ለትውልድ አደራ!!” መሪ ቃል ማክበር ያስፈለገበት ዓብይ ምክንያት አረጋውያን በሀገሪቱ በልማት፣ በባህል፣ በእውቀት፣ በመከባበር፣ የበለጸገ የቤተሰብ እሴቶችን በመፍጠር፣ የአገርን ታሪክና አንድነትን ጠብቆ በማቆየትና ለአዲሱ ትውልድ በማሸጋገር እንዲሁም ለአሀገር የከፈሉትን መስዋዕትነት ለመዘከርና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ ሁለገብ የአረጋውያን ማዕከል ግንባታ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሲ.ኤም.ሲ ጸሀይ ሪል እስቴት ጎን በ6418 ካሬ ሜትር ላይ ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተረገ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ ግንባታው እውን እንዲሆን ሁሉም እንዲረባረብ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር ክቡር አቶ አባ ሙዳ አበበ ኃላሉ ዘመኑ አረጋውያን የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆኑበት እንዲሆን ከልብ ተመኝተዋል፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ጌታቸው ክንፈ በበኩላቸው ማህበሩ የአረጋውያን ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጠው የአጋር አካላትም አስተዋጽኦ እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ማህበረሰብ አቀፍ የድጋፍና እንክብካቤ ድርጅቶች ለልዩ ልዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ አረጋውያን ክብርና ስብዕናን የጠበቀና የወደፊት ተስፋ ሰጪ የሆኑ የመሰረታዊ አገልግሎቶችን ድጋፍ እንዲያገኙና በተስፋ እንዲኖሩ ያለሳለሰ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የገለጹት የሄልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በላቸው ናቸው፡፡
በበዓሉ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የአገር ባለውለታ የሆኑ አረጋውያን፣ የበጎ አድራጎት ተወካዮች እና ሌሎችም የተሳተፉ ሲሆን በዕለቱ ብሔራዊ ሁለገብ የአረጋውያን ማዕከል ግንባታ ዲዛይን ይፋ ተደርጓል፡፡ ለአረጋውያን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት እውቅናና የምስጋና ሰርተፊኬት ተበርክቷል፡፡ በአረጋውን ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች የስራ እንቅስቀሴ አስመልክቶ የተዘጋጀ ኤግዚቢሽንም በክብር እንግዶች ተጎብኝቷል፡፡